Jump to Navigation

“ግብፆች ኢትዮጵያን ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ጋር ማጋጨት ይፈልጋሉ”

አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሲያገኙ፣ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከእንግሊዝ አገር በውኃ ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡

አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ አሁን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለበርካታ ዓመታት የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ ፈቅአህመድ ወደ ወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ዳይሬክተርነት ከተዘዋወሩ አንድ ዓመት ከስድስት ወራትን ሲያሳልፉ፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ከኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል የተነሳውን ፖለቲካዊ አለመግባባት የመቅረፍ ኃላፊነትን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ በመጀመሩ ምክንያት በግብፅ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወቃል፡፡ ይህ የግብፅ ተቃውሞ ከግንዛቤ ጥረት ሊመነጭ እንደሚችል የኢትዮጵያ መንግሥት በመገመት ባቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ባለሙያዎችና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተካተቱበት ቡድን በህዳሴው ግድብ ላይ ጥናት በማካሄድ የጥናቱን ውጤትና ጥናቱን መሠረት ያደረገ ምክረ ሐሳብ ለሦስቱም መንግሥታት ባለፈው ዓመት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህንን ምክረ ሐሳብ በተመለከተና ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ሦስቱ አገሮች የጀመሩዋቸውን ውይይቶችና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ዮሐንስ አንበርብር ከአቶ ፈቅአህመድ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተዋቀረው ቡድን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ጥልቅ ጥናት በማካሄድ በጥናቱ ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳብ ለሦስቱ አገሮች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ የዚህን ምክረ ሐሳብ የተጨመቀ ይዘት ቢያብራሩልኝ፡፡

አቶ ፈቅአህመድ፡- በአጠቃላይ የዚህ ምክረ ሐሳብ ይዘት በአተገባበሩ ዓይነት በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ምክረ ሐሳብ ለኢትዮጵያ ነው የተሰጠው፡፡ ይህም ከግድቡ ደኅንነትና ዲዛይን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲተገብራቸው ነው የሚለው ምክረ ሐሳቡ፡፡ እነዚህም ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ሰነዶችን ወቅታዊ ማድረግና ዲዛይኖችን ወቅታዊ ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ የሚመነጨው ከግንባታው ኮንትራት ባህርይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግንባታው ላይ እየተከተለች ያለው የኮንትራት ዓይነት ኢፒሲ (ኢንጂነሪንግ ፕሮኪዩርመንት ኮንስትራክሽን) ዝርዝር ጥናት፣ ዲዛይን፣ ግዢና ግንባታ ማለት ነው፡፡ ዝርዝር ጥናት እየተጠና ዲዛይኑ እየተሻሻለ ጐን ለጐን ግንባታው የሚከናወንበት የኮንትራት ዓይነት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ጥናቱን ባካሄደበት ወቅት ያየው የመጀመርያውን የግንባታ ሪፖርት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የወጡ ሪፖርቶች አሉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ሪፖርት አለ፡፡ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ሁለተኛ ደረጃ ሪፖርቱን አይቶ ቢሆን ኖሮ በምክረ ሐሳቡ ላይ ያቀረባቸው ሐሳቦች በሙሉ ባልወጡ ነበር፡፡ ስለዚህ የባለሙያዎቹ ቡድን ያነሳቸው ሐሳቦች በሙሉ የኮንትራቱ አካል የሆኑትን ጉዳዮች ነው፡፡ ሌላኛው ምክረ ሐሳብ ሦስቱም አገሮች በጋራ እንዲተገብሩት የቀረበ ነው፡፡ 

ለምሳሌ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠና ‹‹የኃይድሮሎጂ›› (የውኃ ሀብትና የውኃ ፍሰት) ጥናት ተጠንቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግድቡ ሲገነባና ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የውኃ አለቃቀቁ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድራል? ማለትም በተለያዩ የዝናብ ወይም የአየር ሁኔታዎች ውስጥ የሚለውን የሚያሳይ ሞዴል አለ፡፡ ይህ ‹‹ኃይድሮሎጂ ሲሙሌሽን ሞዴል›› ይባላል፡፡ ይህ ሞዴል የተዘጋጀው በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሞዴሎች ጥቁር ሳጥኖች ናቸው ይባላል፡፡ ውስጣቸው የማይታይ፡፡ በዚህም የተነሳ ሦስቱም አገሮች አንድ ላይ ሆነው በተስማሙበት ሞዴል፣ በተስማሙበት መረጃና በተስማሙባቸው ሁኔታዎች ከተሠራ መተማመኑ ይፈጠራል ከሚል እምነት አዲስ ሞዴል በሦስቱ አገሮች በጋራ ቢዘጋጅ የሚል በምክረ ሐሳቡ ተቀምጧል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ወሰን ተሻጋሪ አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ጥናት በኢትዮጵያ በኩል ተዘጋጅቷል፡፡ ይህንን ጥናትና ትንተና ኢትዮጵያ የሠራችው በሁለት መረጃ ላይ ተመሥርታ ነው፡፡ አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥናቱ የተሠራው ሁለት ቦታ ተከፍሎ ነው፡፡ አንደኛው ግድቡ በሚያርፍበት የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የተሠራ ሲሆን፣ ይህ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የባለሙያዎቹ ቡድን ሳይቀር መስክሮለታል፡፡ ሌላኛው ግብፅና ሱዳን ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ የሚመለከት ሲሆን ጥናቱ የተሠራው በሁለተኛ ደረጃ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ምክንያቱም ግብፅና ሱዳን ሉዓላዊ አገሮች ናቸው፡፡ እዚያ ሄደን መረጃ መሰብሰብ አንችልም፡፡ እሱም ብቻ ሳይሆን ጥናቱን ራሱ ማካሄድ አይጠበቅብንም፡፡ ምክንያቱም ስምምነት የለንም፡፡ ስምምነት በሌለብት ማንም አገር አድርጎ በማያውቀው ሁኔታ ኢትዮጵያ ጥናቱን አጥንታለች፡፡ 

ይሁን እንጂ የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ይህንን ጥናት ሦስቱ አገሮች አንድ ላይ ሆነው በአንደኛ ደረጃ መረጃ ላይ በመመሥረት ቢሠሩት፣ በአገሮቹ መካከል ግድቡ ስለሚኖረው ጥቅምና ሊያደርሰው ስለሚችለው ተፅዕኖ መተማመን ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ በጋራ ቢጠና የሚል ምክረ ሐሳብ ነው የሰጠው፡፡ ስለዚህ ምክረ ሐሳቦቹን በዚህ መልኩ በሁለት መክፈል ይቻላል፣ አጠቃላይ ይዘቱም ይህ ነው፡፡ ግድቡን ለመሙላት ስለሚወስደው ጊዜ፣ በእርጥበት ወቅትና በደረቃማ ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው የአሞላል ሥርዓት፣ በግብፅም ሆነ በሱዳን ላይ ተፅዕኖ በማይደርስ ሁኔታ መዘጋጀቱን፣ እንዲሁም በኢትዮጽያ በኩል ሊኖር ስለሚችለው አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በተገቢው መንገድ መጠናቱን የባለሙያዎቹ ቡድን አረጋግጧል፡፡ በአጠቃላይም ከላይ የተጠቀሱትን ምክረ ሐሳቦች ከማቅረቡ በስተቀር፣ የግድቡ ግንባታ ጉልህ ጉዳት በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ እንደማያደርስ የባለሙያዎቹ ጥናት ይገልጻል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ጥናትና ጥናቱን መሠረት ያደረገው ምክረ ሐሳብ ለሦስቱ አገሮች መንግሥታት ቀርቧል፡፡ ምክረ ሐሳቡን በተናጠል ሦስቱ አገሮች እንዴት ነው የተቀበሉት?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት የተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. ሜይ 30 ቀን 2013 ነው፡፡ ከነሰዓቱ ለማስታወስም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ነው፡፡ በእኛ በኩል ለውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር (ለኢትዮጵያ) ሪፖርቱን ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ነው ያስረከብነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጣም ይጠበቅ ስለነበር ነው፡፡ በነጋታው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ የሪፖርቱን ይዘት ሙሉ በሙሉ መቀበሉን፣ ምክረ ሐሳቦቹንና ለኢትዮጵያ በልዩነት የተሰጠውንም ሆነ በጋራ ለሦስቱም አገሮች የቀረቡትን ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ሪፖርቱን ሕዝቡ መረዳት በሚችልበት ሁኔታ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በመተርጎምና በማሳጠር ይፋ እንዲሆንም በኢትዮጵያ በኩል ተደርጓል፡፡ በሱዳን በኩልም ሪፖርቱን እንደሚቀበሉና ለሦስቱ አገሮች የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ከኢትዮጵያና ከግብፅ ጋር ሆነው ለመተግበር መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል፡፡ በግብፅ በኩል ግን የተዘበራረቀ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ሪፖርቱ እንደቀረበ አንቀበልም የሚል መግለጫ ነው የሰጡት፡፡ ሪፖርቱ እውነታውን አላሳየም፣ በሪፖርቱ ውስጥ የኢትዮጵያ እጅ አለበት፣ ስለዚህ አንቀበልም ነው ያሉት፡፡ ከዚያም በኋላ ሁላችንም እንደምናውቀው አላስፈላጊ ንግግሮችን ነው ሲናገሩ የነበሩት፡፡ ይሁን እንጂ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. ጁን 18 ቀን 2013 የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ከመከሩ በኋላ ምክረ ሐሳቡን ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት የባለሙያዎችን ቡድን ሪፖርትን ተቀብለውታል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በግብፅ በኩል ያለው አቋም ዝብርቅርቅና ይህ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሱዳን ከተማ ካርቱም በመገናኘት ድርድሮችን ሲያካሂዱ ነበር?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ድርድር አይደለም፡፡ እያካሄድን ያለነው ውይይት ነው፡፡ ምክንያቱም ለመደራደር የምትደራደርበት ጉዳይ መኖር መቻል አለበት፡፡ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክረ ሐሳቡን ለመተግበር የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ያካሂዱ ነው ያሉት፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማ ምክረ ሐሳቦቹን ለመተግበር የሚያስችል ማዕቀፍ ለመፍጠር ነው፡፡ በአብዛኛውም ውይይቱ ያተኮረው ኮሚቴ ማቋቋም ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ስብሰባ ምክረ ሐሳቡን በጋራ ለመተግበር ሦስቱ አገሮች ተስማምተዋል፡፡ በዚህ መሠረት አተገባበሩን ለመከታተል ኮሚቴ መቋቋም አለበት በሚለው ሐሳብ ላይም በመጀመርያው ስብሰባ ላይ ነው ከስምምነት የተደረሰው፡፡ ከዚያ በኋላ በጣም አከራካሪ የነበረው የኮሚቴው ዓላማ ምን መሆን አለበት የሚለውና የኮሚቴው ስብጥር፣ እንዲሁም የኮሚቴው ተግባርና ኃላፊነት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሠራነው ሥራ ኮሚቴ ማቋቋም ነው፡፡ ኮሚቴ ማቋቋም ድርድር ሊሆን አይችልም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በዚህ ውይይት ላይ ሱዳን እንዳልነበረች ወይም ሚና እንደሌላት ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ በዚህና በውይይቱ ውጤቶች ላይ ማብራሪያ ቢሰጡ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የሱዳን ሚና ጉዳይ ከመጀመሪያውም ጀምሮ ሲንፀባረቅ የነበረ ስህተት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ በጣም ያጐሉ የነበሩት ግብፆች ናቸው፡፡ እዚያም በውይይቱ ላይ በአብዛኛው ልዩነቱ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል እንደተፈጠረ አድርገው ነበር በተደጋጋሚ ሲያነሱ የነበሩት፡፡ ውይይቱ የሦስትዮሽ ነው፡፡ የሱዳን ሚና ግልጽ ነው፡፡ አንዱ የውይይቱ አካልና ባለጉዳይ አገር ነች፡፡ የሱዳንን ትንሽ የሚለየው ስብሰባው የሚካሄደው በአገሯ በመሆኑ ነው፡፡ ስብሰባውን የማመቻቸት ሥራ ይሠራሉ፡፡ አገራቸው ላይ ስለሆነ ስብሰባውን ይመራሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ሱዳን አንድ የውይይቱ አካል ነበረች፡፡ የራሳቸውን ሐሳብ ያነሳሉ፣ በራሳቸው ሐሳብ ላይ አቋም ይዘው ይነጋገራሉ፡፡ ውይይቱ ሲጀመር የተለያየ አቋም ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን አቋም በጣም ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የመነጨው ፍላጎታችን ተመሳሳይ ስለሆነ ነው፡፡ በግብፅ በኩል በግድቡ ዙሪያ መረጃ ማግኘት ይፈልጋሉ፣ ዕውቀት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህም ሥጋትን ይቀንሳል የሚለውን ጉዳይ ያምኑበታል፡፡ ከዚያ በታች ባለው ላይ ግን ልዩነት አለን፡፡ ምክንያቱም በግብፅ በኩል በተቻለ አቅም ግድቡን ማስቆም ነው የሚፈልጉት፡፡ ሱዳን ግን ግድቡ እንዲያልቅ ነው የምትፈልገው፡፡ ወደ ኮሚቴው ስንመለስ ከግብፅ ጋር በመጀመሪያ ልዩነት ነበረን፡፡ በእኛና በሱዳን በኩል ሐሳቡ መተግበሩን መከታተል የኮሚቴው ተግባር ይሁን ነው ያልነው፡፡ ግብፆች ግን ኮሚቴው ነው ምክረ ሐሳቡን መተግበር ያለበት ያሉት፡፡ ኮሚቴው ምክረ ሐሳቡን መተግበር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ምክረ ሐሳቡ የተሰጠው አንደኛው ለኢትዮጵያ መንግሥት ነው፣ በተቀረ ለሦስቱ አገሮች በጋራ ነው፡፡ በዚህ ከተከራከርን በኋላ ግን ሊቀበሉት ችለዋል፡፡ ከዚያ በመቀጠል አከራካሪ የነበረው በኮሚቴው ስብጥር ላይ መግባባት አለመቻላችን ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን የአገሮቹ ባለሙያዎች ብቻ የኮሚቴው አባላት መሆን አለባቸው፣ ምክንያቱም ቀሪ ሥራዎቹ የውጭ አማካሪ አያስፈልጋቸውም የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ኮሚቴው የሚከታተለው ሁለቱን ምክረ ሐሳቦች ነው፡፡ ሁለቱ ምክረ ሐሳቦች ደግሞ የሚጠኑት በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ወይም ድርጅቶች ነው፡፡ በእርግጥ ጥናቱን ሦስቱ አገሮች ከተስማሙ በጋራ ማጥናት ይችላሉ፣ ወይም በተናጥል ማጥናት ይቻላል፣ አቅሙ አለ፡፡ ነገር ግን የበለጠ መተማመን እንዲኖር አማካሪ ድርጅቶች እንዲያጠኑ ተስማምተናል፡፡ ግብፅ ግን በኮሚቴው ስብጥር ውስጥ የሦስቱ አገሮች ውክልና እንዳለ ሆኖ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ይካተቱ የሚል አቋም ይዛ መጣች፡፡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች መካተት የሚጠቅመው ግጭት የሚከሰት ከሆነ ለማግባባት ይጠቅሙ ይሆናል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቀድሞው የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ለአንድ ዓመት ሥራውን በሠራበት ወቅት በአገሮቹ መካከል የነበሩ ልዩነቶችን አንድም ቀን ፈትተው አያውቁም፡፡ እንዲያውም የስብሰባ አዳራሹን ለቀው ነው የሚወጡት፡፡ እኛው ነን ልዩነቶቻችንን ስንፈታ የነበረው፡፡ 

የአቅም ክፍተትን ለመሙላት ከሆነ የውጭ ባለሙያዎቹ የሚያስፈልጉት እያንዳንዱ አገር በራሱ የውጭ አማካሪ መቅጠርና የአቅም ችግሩን መሸፈን ይቻላል አልናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሊያስፈልጉ የሚችሉት ምክረ ሐሳቡ ተጠንቶ የሚቀርበው ሪፖርት ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን፣ በሁሉም አገሮች ተቀባይነት አለው ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነው በሚል ከሆነ ጥናቱ መጀመርየውኑም ቢሆን እንዲጠና የተስማማነው በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ነው በማለት አስረዳናቸው፡፡ በመጨረሻም የእናንተን ምክንያት አስረዱን ብንላቸው ምክንያት ማቅረብ ተስኗቸው የመጀመርያው ውይይት በዚህ ተጠናቀቀ፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 8 እና 9 ቀን 2013 ለመገናኘት ተቀጣጠርን፡፡ በቀጣዩ ስብሰባ ምንም እንኳን በኮሚቴው ስብጥር የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ብቻ እንዲሆኑ በሚለው ቢስማሙም ጐን ለጐን ግን ሌላ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ይቋቋም የሚል ሐሳብ ይዘው መጡ፡፡ እነሱ እንደሚሉት ኮሚቴውም፣ ጐን ለጐን የሚቋቋመው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓናልም የግድቡን ግንባታ ይቆጣጠሩ፣ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን የማቅረብና ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ይኑራቸው፣ እንዲሁም የሚወስኑት ውሳኔ በአገሮቹ ላይ አስገዳጅ ይሁን የሚል የአገሮቹን ሉዓላዊነት የሚፈትን ሐሳቦች አቀረቡ፡፡ ነገር ግን በተደረገ ውይይት ግብፆቹ በስተመጨረሻ አብዛኛውን ሐሳባቸውን አንስተዋል፡፡ የኮሚቴው ዓላማ ክትትል ብቻ እንዲሆን፣ በስብጥሩም ከሦስቱ አገሮች የሚወከሉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲሆኑ፡፡ ተግባርና ኃላፊነቱ ላይም በሁለተኛው ስብሰባ ላይ ተስማምተናል፡፡ በዚህ ስብሰባ መካከል ግን አንድ ሐሳብ ተነስቷል፡፡ ይኸውም ኮሚቴው ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ በሚያደርግበት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ማለትም የውጭ አማካሪ በመቅጠር ምክረ ሐሳቡን እንዲጠና አድርጎ በሚቀርብለት ሪፖርት ላይ መግባባት ካልተቻለ እንዴት ይሆናል የሚል ሐሳብ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ወቅት በኮሚቴው ውስጥ ልዩነት ከተነሳ ለሚኒስትሮቹ ቀርቦ በውይይት በስምምነት ይፈቱታል የሚል ምላሽ ተሰጠ፡፡ ነገር ግን ሚኒስትሮቹ ባይስማሙስ የሚል ሐሳብ ተነሳ፡፡ ሚኒስትሮቹ ካልተስማሙ የሙያ ሐሳብ የሚያቀርብ ዓለም አቀፍ አማካሪ መቅጠር ይቻላል በሚለው ተስማማን፡፡ ይህ አማካሪ ድርጅት ወይም የባለሙያዎች ቡድን ሊቋቋም የሚችለው ሚኒስትሮቹ መስማማት ሳይችሉ ቀርተው ሙያዊ ምክር ለማግኘት መሆኑ ላይ ብንስማማም፣ ግብፆቹ ወደኋላ ተመልሰው አሁን ተቋቁሞ መቀመጥ አለበት አሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ በሎጂክ (አመክንዮ) ደረጃ ስናየው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ከዓመት በኋላ ለሚቀርብ ሪፖርት አሁን ላይ የባለሙያ ቡድን መቅጠርና ማስቀመጥ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በዚህ መግባባት አልቻልንም፡፡ ከዚህ ውጪ የውጭ ባለሙያዎች ፓናል ለማቋቋም በሦስቱ ሚኒስትሮች ስምምነት ሳይሆን አንድም ሚኒስትር ቢሆን አቋቁሞ መላክ ይችላል የሚል ሐሳብ አመጡ፡፡ በዚህ ላይ መስማማት አልቻልንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በዚሁ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ የሱዳን አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነበር?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 4 ቀን 2013 ተሰብሰበን፡፡ ከዚህ ስብሰባ በፊት ከኮሚቴው አመሠራረት ጋር ያልተያያዘ በግብፆች የቀረበ አንድ ሐሳብ ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ የመተማመን ማጐልበቻ መርህ የሚል ነበር፡፡ እኛ በዚህ ሐሳብ ላይ ወይም ይዘው በቀረቡት ባለሰባት ነጥብ መርህ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ አልነበርንም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የስብሰባው ዓላማ ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ ውይይት ነው፡፡ የአጀንዳው አካል አይደለም፡፡ በየአገሮቻችን መንግሥታት ለዚህ የውይይት አጀንዳ አልተወከልንም ወይም ሥልጣን አልተሰጠንም፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ያቀረቡትን ሐሳብ በምንመለከትበት ጊዜ ሐሳቦቹ አንዳንዶቹ ከናይል የትብብር ማዕቀፍ ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡ በተለይ ከውኃ ዋስትና ጋር ባቀረቡት ነጥብ ያስቀመጡት ከትብብር ማዕቀፉ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የናይል ትብብር ማዕቀፍን ፈርማለች፣ ከዚህም አልፋ በሕግ አውጪው አካል አፅድቃለች፡፡ ስለዚህ ይህንን ማዕቀፍ በተመለከተ ከማንም ጋር መነጋገር አትችልም፡፡ የስምምነቱ አካል ካልሆነ አገር ጋር ላለመነጋገር ግዴታ ገብታለች፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በናይል ተፋሰስ ውስጥ ድርድር የሚባል ነገር ስምምነቱ ሲፈረም አብቅቷል፡፡ ስለዚህ የተዘጋ ነገር ነው፡፡ መነሳት ይገባዋል የምትሉ ከሆነም መድረኩ ሌላ ነው ብለን በግልጽ ነግረናቸዋል፡፡ ነገር ግን አልሰሙንም፡፡ በመሆኑም በሦስተኛው የጃንዋሪ ስብሰባ በድጋሚ ለውይይት አቀረቡ፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ፓናል አሁኑኑ ይቋቋም በሚለው ሐሳባቸው፣ እንዲሁም የመተማመኛ ማጎልበቻ መርሆዎች ላይ ለውጥ ሊታይ ባለመቻሉ ስብሰባውን ማስተላለፍ የግድ ሆነ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስብሰባው ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ በግብፅ ሚዲያዎች በኩል እየተነገረ ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ እንዲተላለፍ ተወሰነ ነው የሚሉት?

አቶ ፈቅ አህመድ፡- በኢትዮጵያ በኩል የቀጣይ ቀጠሮ ቀንና ቦታ እንዲወሰን ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ በግብፅ በኩል ውይይቱ መቀጠል እንዳለበት የተስማሙ ቢሆንም፣ ቦታና ጊዜ ለመወሰን ከመንግሥታቸው ጋር መነጋገር እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡ ከስብሰባው አዳራሽ እንደወጡ ወዲያውኑ ሚኒስትሩ ለሚዲያዎች መግለጫ በመስጠት ኢትዮጵያ ውይይቱን አደናቅፋለች ብለዋል፡፡ አገራቸውም ደርሰው ኢትዮጵያ ውይይቱን እንዳደናቀፈች፣ ኢትዮጵያ የግብፅን ራዕይ ካልተቀበለች በስተቀር ዳግመኛ ግብፅ ወደ ድርድር እንደማትገባ ለሚዲያዎች የተናገሩትን ሰምተናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ውይይት እንደሚመለሱ እንደዚሁ ከሚዲያዎች እየሰማን ነው ያለነው፡፡ በእኛ በኩል ውይይቱ መቀጠል አለበት፡፡ ውይይት ካለ ልዩነቶች ይጠባሉ፣ ስምምነት ይፈጠራል፡፡ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ላይ ከዚህ ውጪ መፍትሔ የለም፡፡ መወያየት፣ መነጋገርና ልዩነትን ማጥበብ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እስካሁን ከነገሩኝ የምረዳው ነገር ግብፆች የውጭ ወይም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈልጉ ነው፡፡ ይህንን ለምን እንደፈለጉት እንደባለሙያ መገመት ይችላሉ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ከሒደቱ እንደተረዳነው በምክረ ሐሳቡ መተግበር በላይ ግብፆቹ እየፈለጉ ያሉት የዓለም አቀፍ ፓናል መቋቋምን ነው፡፡ ይህንን የፈለጉበት የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ምናልባትም ሊሆን የሚችለው ዓለም አቀፍ የባሙያዎች ፓናሉን ለሚፈልጉት ዓላማ መጠቀም ነው፡፡ አንደኛ ዓለም አቀፍ ፓናሉን ሐሳቡንም ማስቀየር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ የእነሱን ምስክርነት ሰብስበው ወደሌሎች መድረኮች ለመሄድ አስበውም ሊሆን ይችላል፡፡ በጣም የሚገርመው በኮሚቴው ላይ ለነበረው ልዩነት ማስታረቂያ በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ሐሳቡ በሦስቱ አገሮች ኮሚቴው ይመሥረትና ወደሥራ ይግባ፣ የዓለም አቀፍ ፓናሉን ጉዳይ ሥራው እየተሠራ እንወያይበት የሚል ነበር፡፡ ቢሆንም በግብፅ በኩል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይህ የሚያሳየን ምንድነው ግብፆች በምክረ ሐሳቡ አተገባበር ላይ ብዙም ፍላጎት አለማሳየታቸውን ነው፡፡ እነሱ ሌላ ዓለም አቀፍ ፓናል አቋቁመውና ፓናሉን አሳስተው ወይም በፈለጉበት አቅጣጫ ሄደው የእነሱን ምስክርነት ይዘው ወደፈለጉበት ሌላ መድረክ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ በእኛ በኩል ፓናሉ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ ቢሆንና ቢቋቋም ችግር የለብንም፡፡  ከዚህ ቀደም በነበረው ፓናል ውስጥ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲወከሉ ሐሳቡን ያቀረበችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ አሁን ግን ስለማያስፈልግ አልተቀበልነውም፡፡ ወደፊትም አንቀበለውም፡፡ ሁለተኛው ዙር ውይይት ከመካሄዱ በፊት የግብፅ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር ለሱዳኑ አቻቸው በሰጡት ቃል መሠረት ግብፅ የግድቡ ግንባታ ይቁም የሚል ሐሳብ ዳግመኛ እንደማታነሳ፣ እንዲሁም ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን የውጭ ብድር ለማስከልከል አትጥርም ብለው ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የኢትዮጵያ ልዑክ ይኼንን በመስማት የግብፅን የተደበቀ ዓላማ እንድንቀበል ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ንግግራቸው ውስጥ የተደበቁ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ ግብፆች ዓለም አቀፍ ፓናሉ ይቋቋም ከሚለው ሐሳብ ውጪ ይዘው የመጡት መተማመኛ ማጎልበቻ መርህ የሚል ሰባት ነጥቦችን ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦችን ያቀረቡበት ምክንያት በሁለት ዓላማዎች ነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ዋስትና እንድታከብር ነው፡፡ ዋስትና በእነሱ ትርጓሜ አሁን የሚያገኙት የውኃ መጠንና ወደፊት የሚፈልጉት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር ብትጀምር በናይል የትብብር ማዕቀፍ የገባችውን ግዴታ አፈረሰች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወዲያውኑ ስምምነቱን ከፈረሙ የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ኢትዮጵያን ማጋጨትና ስምምነቱን ማዳከም ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ እኛ ይህንን ነገር ጠንቅቀን ስለምንረዳ አልተቀበልነውም፡፡ ውድቅ እንዲሆን ነው ያደረግነው፡፡ ሌላኛው የአካሄድ ስልታቸው ኢትዮጵያ የማትቀበላቸውን ነገሮች እየለዩ ኢትዮጵያ ባልተቀበለች ቁጥር ውይይቱን እያደናቀፈች እንዳለች ማስፈረጅ ነው፡፡ ለምሳሌ የግድቡን ግንባታ እንቆጣጠር ሲሉ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ያውቃሉ፡፡ ለምንድነው የሚያነሱት ታዲያ? ኢትዮጵያ አልቀበልም የምትላቸው ነጥቦች እየበዙ ሄደው ኢትዮጵያ ውይይቱን አሰናከለች ለሚል ርካሽ ዓላማ ነው እየተጠቀሙበት ያለው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሱዳን ለዘመናት ከግብፅ ጎን የተሰለፈችና የግብፅን አቋም ስታራምድ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፏ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው፡፡ ሱዳን የአቋም ለውጥ ያደረገችው ለምን ይመስልዎታል?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ይህንን ለመመለስ ወደኋላ መመለስና ብዙ ነገር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. የ1929 ስምምነትን እንውሰድ፡፡ ይህ ስምምነት በታላቋ ብሪታኒያና በግብፅ መካከል ነው የተደረገው፡፡ ታላቋ ብሪታኒያ ሱዳንን ወክላ ነው የፈረመችው፡፡ በዚያ ስምምነት መሠረት ለሱዳን የተሰጠው የውኃ መጠን አራት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ነው፡፡ የተቀረው ውኃ ለግብፅ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግብፅ ሱዳን ውስጥ ግድብ የመገደብ ሥልጣን አላት፡፡ ሱዳን የተፈቀደላትን ውኃ መጠቀም ስትፈልግ ከግብፅ ፈቃድ ማግኘት አለባት፡፡ እናም ይህ በፍፁም ፍትሐዊ የሆነ ስምምነት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ. በ1956 ሱዳኖች ነፃነታቸውን ሲያውጁ ይህንን ስምምነት አንቀበልም በማለታቸውና ለመደራደርም ፈቃደኛ ስላልነበሩ እ.ኤ.አ. በ1957 ሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደ፡፡ ከዚህ መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ የግብፅ እጅ እንዳለበት ይነገራል፡፡ ወዲያው አዲሱ የሱዳን መንግሥት ከግብፅ ጋር ተደራድሮ እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት በሱዳንና በግብፅ መካከል ተፈረመ፡፡ ይህንን ስምምነትም ስናይ ከዚያኛው የተለየ አይደለም፡፡ ምናልባት ለሱዳን የተመደበው የውኃ መጠን ከፍ ያለ ቢሆንም ይህ የውኃ መጠን ግን ከግብፅ ተቀንሶ አይደለም የተሰጠው ማለት ይቻላል፡፡ በፊት በመረጃ ደረጃ ያልታወቀ የውኃ መጠን ስለተገኘ ብቻ ነው ሱዳን እንድታገኝ የተደረገው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሱዳን እስካሁን ግማሹንም አልተጠቀመችም፡፡ ሱዳኖች ተጨማሪ ውኃ መጠቀም በፈለጉ ጊዜ ግብፆች ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የመሮዌ ግድብ አልቋል፡፡ አራት ዓመታት ሆኖታል ከተጠናቀቀ፡፡ ነገር ግን ሱዳን የግብፆችን ፈቃድ ጠይቃ እስከዛሬ ፈቃድ አላገኘችም፡፡ ለምሳሌ የሮዜሬስ ግድብን ከፍታ ለመጨመር ሱዳን ፈቃድ ብትጠይቅም እስከዛሬ ድረስ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ስለዚህ ሙሉ በሙሉ የተስማሙበትን ውኃ እንዳይጠቀሙ እየከለከሏቸው ነው፡፡ የግብፅ እጅ ሱዳን ውስጥ በጣም ተንሰራፍቶ ነው ያለው፡፡ በሚኒስቴር ደረጃ ከሱዳን ይልቅ ለግብፅ የሚያግዙ ሚኒስትሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ መከላከያ ሚኒስቴርና ደኅንነት ተቋማት ውስጥ በጣም ተንሰራፍተው ነው ያሉት፡፡ ሱዳኖች ከራሳቸው ይልቅ ለግብፅ እንዲያስቡ ተተብትበው የቆዩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ በተለያየ ሁኔታ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ጉዳዮች፡፡ አሁን ግን ሱዳኖች እየነቁ ነው ያሉት፡፡ ለአገራቸው ማሰብ ሲጀምሩ የትኛው ነው የሚጠቅመው የሚለውን መለየት ችለዋል፡፡ ሱዳኖች በኢትዮጵያ በኩል ግድብ ሲገነባ ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ እየተረዱ ነው ያሉት፡፡ ለምሳሌ የተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብን መውሰድ ይቻላል፡፡ የሱዳን ካሸምአልገርባ የተባለ ግድብ ተከዜ ወይም በሱዳኖች ስያሜ አትባራ ወንዝ ላይ መሠረት ተደርጎ የተገነባ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡ ይህ ግድብ በደለል ተሞልቶ የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በራሷ በኩል ተከዜ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባቷ የሚሄደውን ደለል አቁሞላቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ይጥለቀለቁ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ቆሟል፡፡ ወንዙ ለሦስት ወራት ብቻ ነው ከዚህ ቀደም ይፈስ የነበረው፣ አሁን ግን ዓመቱን ሙሉ ይፈሳል፡፡ በዚህም አርሶ አደሮቻቸው መስኖ እያስፋፉ ነው ያሉት፡፡ እናም ከፍተኛ ጥቅም ነው እያገኙ ያሉት፡፡ እዚህ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ነው ያለው፣ ከዚህም ጥቅም እናገኛለን ነው የሚሉት፡፡ ከዚህ ውጪ ሱዳኖች ቁጭ ብለው ሲያዩ ወደ አገራቸው የሚፈሰው ውኃ የሚመነጨው ከኢትዮጵያና ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ብቻ ነው፡፡ ይህንን ውኃ ዘላቂ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀም የሚችሉት ከኢትዮጵያና ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር ብቻ ሲቆሙ መሆኑን ተረድተውታል፡፡ በአጠቃላይ ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ ብለው ነው ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙት፡፡ ይህ የጥቅም ጉዳይ ነው፣ ይህ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፣ ይህ ሥልታዊ የሆነ ግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ ፖለቲካዊ ጉዳይ አይደለም ግብፆች እንደሚያነሱት፡፡ ግብፆች የሚሉት ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ያዘነበለችው ሱዳን የምትደግፈው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከግብፅ በመባረሩ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሱዳኖች ወደ ናይል የትብብር ማዕቀፍ የተመለሱት ወይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የጀመሩት በፕሬዚዳንት ሙባረክ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ አይደለም ለጥቅማቸው ሲሉ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሱዳን የአቋም ለውጥ ለኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብና ተያያዥ ለሆነው የዓባይ ፖለቲካ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ኢትዮጵያ በናይል (ዓባይ) ውኃ የመጠቀም መብት አላት፡፡ ይህንን ሉዓላዊ መብቷን ምንጊዜም አሳልፋ አትሰጥም፡፡ ይህ ሉዓላዊ መብት ግን ምንጊዜም አብረው የሚታዩ ሁኔታዎች አሉት፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች  ዓለም አቀፋዊ አንድምታ አላቸው፡፡ እኛም የምናምንባቸው ናቸው፡፡ ይህም ማለት እኛ ውኃውን ስንጠቀም ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ተጠቅማ ሌሎች እንዲጎዱ አንፈልግም፡፡ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲሰፍን እንፈልጋለን፡፡ በማንም ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት እንዲደርስ አንፈልግም፡፡ ትብብር እንፈልጋለን፡፡ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ወንዞች ሁሉ የሚገቡት ወደ ሱዳን ነው፡፡ ሱዳን ረዥም ድንበር የምትካለለን ጎረቤት አገር ናት፡፡ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ በድንበሩ አካባቢ ላይ ሕዝብ ሰፍሯል፡፡ በሕዝቦቹ መካከል ደግሞ መተሳሰር አለ፡፡ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ  መተሳሰር አለ፡፡ ስለዚህ ከሱዳን ጋር የሚኖረን ግንኙነት ከማንም በላይ ይጠቅመናል፡፡ ከሱዳን ጋር ያለን የድንበር ግንኙነት ርዝመቱ ሲታይ ከማንም ጋር እንደዚህ ዓይነት ሰፊ የድንበር ግንኙነት የለንም፡፡ በመንገድ ተገናኝተናል፣ በአየር ተገናኝተናል፣ በባቡር ልንገናኝ ነው፣ ከሁሉም በላይ ግን በውኃ ተሳስረናል፡፡ ስለዚህ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት ለኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ ሥልታዊ ጠቀሜታ አለው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በግብፅ በኩል በተደጋጋሚ እየተሰማ የሚገኘው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት እንዲከበርላት ወይም ታሪካዊውን የዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷ እንዲጠበቅላት ነው፡፡ የቅኝ ግዛት ስምምነትና ታሪካዊ የመጠቀም መብት በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት አላቸው?

አቶ ፈቅ አህመድ፡- ወደ ስምምነቶቹ ስንመጣ ዋናው እ.ኤ.አ. በ1929 የተደረገው ስምምነት ነው የቅኝ ግዛት ስምምነት የሚባለው፡፡ ይህ ስምምነት በግብፅና በታላቋ ብሪታኒያ መካከል ነው የተደረገው፡፡ ታላቋ ብሪታኒያ ሱዳንና የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ማለትም ኬንያ፣ ኡጋንዳና የቀድሞዋ ታንጋኒካን (ታንዛኒያ) ወክላ ነው ስምምነቱን ከግብፅ ጋር የፈረመችው፡፡ የቅኝ ግዛት ዘመን እያበቃ፣ እያንዳንዱ አገር ነፃ እየወጣ ሲመጣ ይህንን ስምምነት ሁሉም ውድቅ አድርገውታል፡፡ ስለዚህ አገሮች ነፃ መውጣት ሲጀምሩ የራሳቸውን ሕግ የማውጣት፣ የሚስማማቸውን የመቀበል፣ ያልተስማማቸውን ደግሞ ውድቅ አድርገዋል፡፡ በተለይ በወቅቱ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጁሊየስ ኔሬሬ አዲስ ዶክትሪን አውጥተው ነበር፡፡ ‹‹ዘ ኔሬሬ ዶክትሪን›› በሚል ነበር የሚታወቀው፡፡ በዚህ ዶክትሪን መሠረት አንድ አገር በቅኝ ግዛት ሥር እያለ ቅኝ ገዢው የገባው ውል (ስምምነት) አገሪቱ ፈልጋ ያንን ስምምነት ወቅታዊ ካላደረገችው በስተቀር፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ውድቅ ይሆናል በሚል ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ይህንን ዶክትሪን ኬንያና ኡጋንዳም ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ይህ ዶክትሪን በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ስምምነቱን ውድቅ አድርገውታል ማለት ነው፡፡ ሌላዋ ሱዳን ነች፡፡ ሱዳንም ነፃ ስትወጣ የቅኝ ግዛቱን ስምምነት ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ ከዚያም የ1959 ስምምነትን መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ ስምምነት በግብፅና በሱዳን መካከል ነው የተፈረመው፡፡ ስለዚህ የሁለቱ አገሮች ጉዳይ እንጂ ሌሎቹን አገሮች አይመለከትም፡፡ ግን ዝም ብለን ይህንን ስምምነት ብንመለከት እንኳን ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ሌሎቹን የተፋሰሱ አገሮች አላሳተፈም፡፡ እንዲያውም በዚህ ስምምነት ለመሳተፍ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባ አንቀበልም ብለዋል፡፡ የሆነው ሆኖ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገውን ስምምነት በራሱ እንኳን ብንመለከተው ፍትሐዊ አይደለም፡፡ አንድ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት በውል ሰጪና በውል ተቀባዩ መካከል ሚዛናዊ የሆነ መብትና ግዴታ መጣል መቻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በማንኛውም ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ ስምምነት እኮ ለሱዳን 18 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ፣ ለግብፅ 55 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ሲሰጥ በተጨማሪ ግብፅ በትነት ለምታባክነው በሚል አሥር ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የውኃ መጠን የሚሰጥ ነው፡፡ ሌላኛው የስምምነቱ ነጥብ ሱዳንና ሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃውን በመጠቀም ልማት ማካሄድ ሲፈልጉ በመጀመርያ ከግብፅ ፈቃድ ይጠይቁ ይላል፡፡ ግብፅ ግን ከማንም ፈቃድ እንድትጠይቅ ያስቀመጠው ግዴታ የለም፡፡ ስለዚህ ኢፍትሐዊ ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም፡፡ ግብፅ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ሄዳ ግድብ የመሥራትን መብት ስምምነቱ ይሰጣታል፡፡ ለምሳሌ ሱዳን ውስጥ ጀበል አውሊያ የሚባል ግድብ አለ፡፡ ይህንን ግድብ የገነባችው ግብፅ ነች፡፡ ኡጋንዳ ውስጥ ኦዬንፎልስ የሚባል ግድብ አለ ግብፆች ናቸው የገነቡት፡፡ እስካሁንም የሚቆጣጠሩት ግብፆች ናቸው፡፡ ሌሎቹ አገሮች ግን ግብፅ ውስጥ ሄደው መገንባት ይቅርና ግብፅ የምትሠራውን እንድታሳውቃቸው መጠየቅ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በምንም ዓይነት ሚዛናዊ አይደለም፡፡ በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ደግሞ አስገዳጅነት የለውም፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ ታሪካዊ የመጠቀም መብት የሚሉት መከራከሪያ ነጥብ አለ፡፡ ይህ ታሪካዊ መብት የሚባለው በማንኛውም ዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ታይቶ አይታወቅም፣ ተቀባይነትም የለውም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልክቶ የታወቁና ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎች አሉ፡፡ እነዚህ መርሆዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተካተቱና የተጠቀሙባቸው ናቸው፡፡ እነኚህም ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ጥንቃቄ የሚሉ ናቸው፡፡ እነኚህ መርሆዎች እ.ኤ.አ. በየትኛውም ዓለም ተቀባይነት ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ መርሆዎች እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 ስምምነቶች ውስጥ አልተካተቱም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ስምምነቶች ኢፍትሐዊ ናቸው፡፡ ወዳቂም ነው የሚሆኑት፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከጠቀሷቸው ተቀባይነት ያላቸው ዓለም አቀፍ መርሆዎች መካከል ዋነኛው በሌላ አገር ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ጉልህ ጉዳት የሚለው እንዴት ነው የሚመዘነው? ለአንዱ ጉልህ ጉዳት፣ ለአንዱ ደግሞ ጉዳት ላይሆን ይችላል፡፡ ይህንን ሚዛን የጠበቀ ውሳኔ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ጉልህ ጉዳት አለማድረስ ስለሚለው መርሆ ለመናገር በመጀመሪያ በአገሮች መካከል ስምምነት ሊኖር ይገባል፡፡ ጉልህ ጉዳት ምንድን ነው የሚለውን ቁጭ ብለን ተነጋግረን መስማማት ይጠበቅብናል፡፡ አንዱ አገር እኮ የውኃውን 90 በመቶ ተጠቅሞ ጉልህ ጉዳት አላደረስኩም ሊል ይችላል፡፡ ስለዚህ ስምምነቱ መኖር አለበት፡፡ ስምምነቱ በሌለበት ሁኔታ በአብዛኛው የሚደረገው ለምሳሌ ያህል አንዱ ጥቅምን ማወዳደር ነው፡፡ ለአንዱ አገር የሚሰጠው ጥቅም አለ፣ ሌላኛው አገር ላይ ደግሞ የሚያመጣው ተፅዕኖ አለ፡፡ ሁለቱን ማወዳደር ይቻላል፡፡ ሌላኛው ተፅዕኖ ቢኖርም ጥቅም ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የውኃ ፍሰት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን የውኃው አመጣጥ (የሚመጣበት ጊዜ) ሊጨምር ይችላል፡፡ ስለዚህ ተፅዕኖው በሌላ ጥቅም እየተካካሰ ሊሄድ ይችላልና በዚህ መልኩ ነው እየታየ የሚሄደው፡፡ አለበለዚያ ግን ጉልህ ጉዳት አለ ወይስ የለም የሚለውን አገሮቹ ቁጭ ብለው ተነጋግረው መስማማት አለባቸው፡፡ ይህ ከተከሰተ ጉልህ ነው፡፡ ይህ ካልተከሰተ ደግሞ ጉልህ አይደለም መባባል መቻል አለባቸው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውኃ ይጠራቀማል፡፡ ግድቡ እስከሚሞላ ድረስ አስዋን ላይ ጉዳት ያደርሳል ነው ግብፆች የሚሉት፡፡ ግብፅ አስዋን ላይ የምታጠራቅመው የውኃ መጠን ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚሆናትን ነው፡፡ ይህ ውኃ በረሃ ላይ ተጠራቅሞ ለትነት ከሚጋለጥና ከሚባክን የተወሰነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጥ እንዲጠራቀም ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግብፅ በቂ ውኃ አስዋን ግድብ ውስጥ ይኖራታል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚጠራቀመው ውኃ ኃይል አመንጭቶ የሚሄደው ወደዚያው ነው፡፡ ስለዚህ የሚያመጣው ችግር የለም፡፡ ሌላው የህዳሴ ግድብ ውስጥ ውኃ ሲጠራቀም በትነት የሚጠፋ ውኃ አለ፡፡ ይህ የውኃ መጠን ግን ከበቂ በላይ ይካካሳል፡፡ የህዳሴ ግድብ በሌለበት ውኃው ሱዳን ውስጥ ሲደርስ ጎርፍ ነው የሚሆነው፡፡ ጎርፍ ሆኖ አገር አጥለቅልቆ ወደ መሬት ሠርጎ ነው የሚጠፋው፡፡ ይህ በግድቡ ምክንያት ይቀረፋል፡፡ ግብፅም ሲደርስ ጎርፍ የሚያስከትል በመሆኑ አስዋን ግድብን በጎን በኩል በማስተንፈስ ወደ በረሃ ነው የሚለቁት፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ እ.ኤ.አ. በ2004 ወደ በረሃ የለቀቁት 42 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ነው፡፡ ይህ ግድብ ካለ ግን እነዚህን ነገሮች በመቀነስ የሚጠፋውን ውኃ ያካክሳል፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ግድብ ሲሞላ የአስዋን የውኃ መጠን ከፍታ ይቀንሳል፡፡ ከፍታው በቀነሰ ቁጥር ለፀሐይ የመጋለጥ ዕድሉ ዝቅተኛ በመሆኑ በትነት የሚጠፋው የውኃ መጠን ይቀንሳል፡፡ በዚህም የተነሳ ግድቡ ከተሠራ በኋላ ወደ ግብፅ የሚደርሰው የውኃ መጠን ይጨምራል የሚል ጥናት ነው በኢትዮጵያ በኩል ያለው፡፡ ይህ ማለት ግድቡ ጉልህ ጉዳት አያደርስም ማለት ብቻ ሳይሆን ይጠቅማቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን የምንለው እኛ ነን፡፡ በስምምነት ደረጃ ከሄድን ግን ስምምነት ስለሌለን በዚህ ጉዳይ መነጋገር ያስፈልጋል ከማለት የዘለለ ማለት አይቻልም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በዓባይ ፖለቲካ ዙሪያ እስካሁን ያለውን ሁኔታ በመገምገም ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት ገጽታ ሊይዝ ይችላል ብለው ይገምታሉ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የግብፅን አቅጣጫ ወይም አቋም እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲያውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግብፅ በኩል ስንት መንግሥት ተቀየረ የሚለውን ብቻ ማንሳት እንችላለን፡፡ ግድቡ ሲጀመር ፕሬዚዳንት ሙባረክ ነበሩ፣ ከዚያ የሽግግር መንግሥት፣ ከዚያ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ፣ እንደገና የሽግግር መንግሥት ነው ያለው፡፡ በሚቀጥለው ቋሚ መንግሥት ይመጣል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ ከዚያ በኋላ ምን እንደሚመጣ አናውቅም፡፡ ስለዚህ የግብፅ አቋም ይህንን ሊመስል ይችላል፣ ወደዚህ ሊሄድ ይችላል ለማለትና ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ቋሚ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በሽግግር ላይ ያለው መንግሥት ሥልጣኑን ለማራዘም ምንድነው የሚጠቀመው የሚለውን ለመተንበይ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በረዥም ጊዜ ግን ግብፅ አንድ አማራጭ ብቻ ነው ያላት፡፡ ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር ተባብራ፣ ተነጋግራና ተስማምታ መሥራት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ውኃው ሙሉ በሙሉ የሚመጣው ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ነው፡፡ ግብፅ በትብብርና በስምምነት እውነተኛ ትብብር አሳይታ ወደ ስምምነት ከመጣች ተጠቃሚ ነው የምትሆነው፡፡ 

 

Tags:


Main menu 2

Article | by Dr. Radut